Monday, February 23, 2015

የቀድሞው ቴሌኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ከእስር ተፈቱ




በፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የሙስና ክስ ተመሥርቶባቸው ጥፋተኛ ከተባሉ በኋላ የዘጠኝ ዓመት ከስድስት ወራት በላይ እስራትና የገንዘብ ቅጣት ተወስኖባቸው የነበሩት የቀድሞው የኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ተስፋዬ ብሩ፣ የካቲት 12 ቀን 2007 ዓ.ም. በአመክሮ ከእስር ተፈቱ፡፡
ኮርፖሬሽኑ በ1997 ዓ.ም. አውጥቶት የነበረውን የሞባይል ማስፋፊያ ፕሮጀክት ጨረታና የተለያዩ ዕቃዎች ግዥ ያላግባብ የስዊድን ቴሌኮም ኩባንያ ኤሪክሰን እንዲያሸንፍ አድርገዋል ተብለው፣ ዶ/ር ተስፋዬን ጨምሮ 11 ከፍተኛ የኮርፖሬሽኑ ኃላፊዎችና 13 ግለሰቦች ላይ በሰኔ ወር 2000 ዓ.ም. የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ክስ መሥርቶ ነበር፡፡ በሌላ ፋይል የብሮድባንድ አገልግሎት ላይ ሙስና ፈጽመዋል በሚል ሁለተኛ ክስም ቀርቦባቸው ነበር፡፡ 
 ከ600,000 በላይ ለሚሆኑ ደንበኞች አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ ለኤሪክሰን ከተሰጠው 47.4 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ፕሮጀክት 9.1 ሚሊዮን ብር ግዥ መፈጸሙ በክሱ ተገልጾ ነበር፡፡ ግዥው ከመፈጸሙም በተጨማሪ ፕሮጀክቱ በመጓተቱ ምክንያት መንግሥት ከ1.5 ቢሊዮን ብር በላይ ማጣቱን ኮሚሽኑ በወቅቱ ለፍርድ ቤቱ ማስረዳቱ ይታወሳል፡፡
በሙስና ተከሰው ከታሰሩት 24 ሰዎች መካከል ዶ/ር ተስፋዬን ጨምሮ 16 ተከሳሾች ጥፋተኛ ተብለው በእስራትና በገንዘብ ተቀጥተዋል፡፡ ዶ/ር ተስፋዬ የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው የተሾሙት በጥር ወር 1995 ዓ.ም. ሲሆን፣ በግንቦት ወር 1998 ዓ.ም. ከኃላፊነታቸው ተነስተው የጠቅላይ ሚኒስትሩ (አቶ መለስ ዜናዊ) አማካሪ ሆነው ተሹመው ነበር፡፡ ለዶክትሬት ዲግሪ ትምህርት ወደ ጀርመን አገር ሄደው የነበሩት ዶ/ር ተስፋዬ፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካይነት ተጠርተው ወደ ኢትዮጵያ እንደተመለሱ ለእስር መዳረጋቸው ይታወቃል፡፡ በእስር ላይ እያሉ የዶክትሬት ዲግሪያቸውንም አግኝተዋል፡፡ 
ዶ/ር ተስፋዬ በ2000 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሲሆን፣ በ2003 ዓ.ም. ጥፋተኛ መባላቸው ይታወሳል፡፡ ዶ/ር ተስፋዬ የእስር ጊዜያቸውን አጠናቀው የካቲት 12 ቀን 2007 ዓ.ም. ከቤተሰቦቻቸው ጋር ተቀላቅለዋል፡፡

No comments:

Post a Comment