ታሪኩ ደሳለኝ
ከ41 ቀን በኋላ ተሜን መጠየቅ ይቻል ይሆን ወይ የሚለው ተስፋችን ከፍ ብሎ በማለዳ ነው ከጋዜጠኛ ዳዊት ታደሠ ጋር ዝዋይ እስር ቤት የደረስነው፡፡ ተስፋችን ከፍ ያለበት ትላንት ማታ የሰብዊ መብት ኮሚሸን መርማሪዎች እኔና ዳዊት ጋ ደውለው እኛ እያለን ኑ መጠየቅ ትችላችሁ ስላሉን ነበር፡፡

ይህን ተስፋ ይዘን እስር ቤቱ ደረስን፡፡ ለጠባቂ ወታደሮቹ የሚያስፈልገውን መረጃ ሰጥተን ልንገባ ስንል ታሪኩ እንጂ ዳዊት አይገባም በማለት ንትርክ ጀመሩ “ለምንድን ነው የማልገባው” አላቸው ባለሬዲዮው ወታደር “ስለማትገ” “ለምን” “በቃ አትገባም” ወታደሩን አያናገርነው ጥሎን ሄደ፡፡ ዳዊት አንዴ እኔን አንዴ የያዝኩትን ስንቅ እየተመለከተ “አንተ ግባ” አለኝ፡፡ ላስረዳው ስል እንደ ታላቅ ወንድም ተቆጣኝ፤ ስንቁን ይዤ ገባሁ፡፡
ተመስገን የሚጠየቀው ከሌሎች እስረኞች የተለየ ቦታ ነው፡፡ የመጠበቂያው ሥፍራ ላይ እያለሁ እስከዛሬ አይቼው በማለውቀው ሁኔታ ሁለት ወታደሮች መጥተው ከአጠገቤ ቆሙ፡፡ ከትንሽ ደቂቃ በኋላ ደግሞ ተሜ በስድስት ወታደሮች ተከቦ ብቅ አለ፡፡ ልቤ ቀጥ ሲል ይሰማኝል፡፡ ወንድሜ የናፈቀኝ ይሄን ያሃል ነው? አይኔን ከተሜ ላይ ሳላነሳ አጠገቤ እስኪደርስ ቆሜ ጠበኩት፡፡ እንደሁልጊዜው አቅፎ ግንባሬን ሳመኝ፡፡ እንዳላለቅስ ያደረገኝ ነገር ህይወት እንዳጠፋ፣ በግፍ ህፃናትን እንደደፈረ ሰው በ6 ወታደሮች መካከል፤ ከ41 ቀናት በኋላም ሳየው ካለበት የመንፈስ ከፍታ ጥቂት እንኳ ጎንበስ አለማለቱ አኮራኝ፡፡ ከእቅፉ እንደወጣሁ “እማዬ” እንዴት ነች አለኝ፡፡ “እማዬ” ደና ናት አልኩት…. ለማለት ያህል…
ስለሰሞኑ የባይነ መረብ ዘመቻ ነገርኩት፡፡ በፈግግታ ልባዊ ወዳጅነትን፣ ስስትንና ወንድማዊነትን ላሳዩት ሁሉ አመሰግናለሁ አለኝ፡፡ “እኔ እንዳልጠየቅ የከለከሉበት ምክንያት ምንድነው ብለው ነገሯችሁ” አለኝ፡፡ “ምን አገባችሁ” ብቻ እንደሆነ ነግርኩት፡፡
ህመምህ እንዴት ነው? አልኩ “በጣም አሞኛል፤ ጀርባዬ እብጠቱ ጨምሯል በጀርባዬ መተኛትም ሆነ መደገፍ አልችልም” አለኝ፡፡ እምለው የለ ዝም አልኩ፡፡ “በግራ ጆሮዬ ለማዳመጥ እየተቸገርኩኝ ነው” አለኝ መተውህ ነው? ስለው ካጀቡት ወታደሮች አንዱ “በቃችሁ ተነሱ” ሲለን ከጀርባዬ ባለዘንባባ ማዕረግ ያለው ወታደር እና የሰብዊ መብት ኮሚሽን መርማሪ መጡ፡፡ የኮሚሽኑ መርማሪ ከአንድ ቀን በፊት እኛን ቀድመው መድረሱን ልብ አልኩኝ፡፡ መርማሪውም እንዴት ነው ተመስገን ሲለው? ተሜም “እንደምታየው ነው ሁለት ሆነው መጥተው አንዱን ነው ያስገቡት፣ ማረሚያ ቤቱ ከሌሎች እስረኞች በተለየ መልኩ ከኔ ጋር ምን እንዳለው አላውቅም፤ ህክምና አላገኘሁም ማንም እንዳይጠይቀኝ ተደረጎል ህግ እየጣሱ ነው” ሲል መርማሪው ምንም ሳይናገር ሄደ፡፡ በለዘንባባ ማዕረግ የታቀፈው ወታደርም በንቀት ሲያየው ተሜም በኩራት አየው፡፡ ወዲያው ወታደሮቹ አዋክበው አስነሱት፡፡ እኔም ደና ሁን ብዬው ሄድኩ፡፡ አልቻልኩምና ዞርኩ ለ6 ታጅቦ እየሄደ ነው፡፡ ወይ ጉድ.. ህመሙ ያለበትን ሁኔታ እያሰብኩ ወጣሁ፡፡
ተሜን በማየቴ ደስተኛ ብሆንም ከሱ የሰማሁት እና በአይኔ ያየሁት ሁኔታ አሳስቦኛል፡፡ ወንድሜን ለማየት 41 ቀናት አስፈልገዋል፡፡ ለህክምናውስ?
No comments:
Post a Comment